አንድ አባት ከባሕር ማዶ ሪፖርት ይጠባበቃል። ሪፖርቱ ክፉ አይደለም፤ አቴንስ ውስጥ ያለውን ልጁን ያመሰግናል — ምስጋናው ግን አንድ ቃል ይዟል፦ «እስካሁን»። አባትየው መልስ ላከ — ደብዳቤ ሳይሆን መጽሐፍ። የጻፈው ከአራት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው፤ የጻፈበት ወራት ደግሞ ሕይወቱን ሊያስከፍሉት የሚችሉ ንግግሮች እየተናገረ የነበረባቸው ወራት ናቸው። በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ስሙ በአደባባይ ግድግዳ ላይ ተለጠፈ፤ ወታደሮች ደረሱበት። መጽሐፉ የሚጠይቀው አንድ ጥያቄ ነው፦ ትክክለኛው ነገርና አዋጭ የሆነው ነገር ወደ ተለያየ አቅጣጫ በሚጐትቱበት ቀን ምን ይደረግ? መልሱ ደግሞ እንዲህ ያለ ቀን የለም የሚል ነው። ታዲያ መልሱ ይቆማል? እናም መጽሐፉ የተጻፈለት ልጅ ምን ሆነ?
ክፍል 1 — መልሱ ደብዳቤ አልነበረም (ሳባ)
* «እስካሁን» ያለው ሪፖርት — 44 ዓ.ዓ.፣ ጸደይ፣ አቴንስ። Leonides የተባለ ሰው ደብዳቤ ይጽፋል። ደብዳቤው ወደ ሮም ይሄዳል፤ እዚያ የቤተሰቡ ወዳጅ Atticus ተቀብሎ ለአባትየው ያስተላልፈዋል። ጥያቄው አንድ ነው፦ ወጣቱ ትምህርቱን እየተከታተለ ነው ወይስ ገንዘቡን እያባከነ ነው? ሪፖርቱ ክፉ አይደለም፤ ወጣቱን ያመሰግናል። ምስጋናው ግን አንድ ቃል ይዟል፦ «እስካሁን»
* ሁለቱ Marcus — ወጣቱ ሃያ ዓመት ገደማ ነው፤ ስሙ Marcus። አባቱ Marcus Tullius Cicero — የሮም ጠበቃ፣ ፖለቲከኛና ጸሐፊ። አባትየው ሲጽፍ ስሙን ወደሚሸከመው ሰው እየጻፈ ነበር
* አባትየው ያንን ቃል አልወደደውም — ለ Atticus መልሶ ሲጽፍ «ይህ የሚተማመን ሰው ምስክርነት አይደለም፤ የሚሰጋ ሰው ምስክርነት ነው» አለ። ከሳምንታት በኋላ ከአቴንስ የደረሱት ሌሎቹ ደብዳቤዎች ልጁን በሙሉ ልብ አሞገሱት። Leonides ግን «እስካሁን» ከሚለው ቃሉ ፈቀቅ አላለም
* ደብዳቤው ወደ አባቱ አልሄደም — የልጁ ደብዳቤ እስከ ዛሬ አለ፤ የተጻፈው ግን ለ Tiro ነው። Tiro የ Cicero ጸሐፊ፣ ቀደም ሲል የቤቱ ባሪያ የነበረና ነጻ የወጣ ሰው ነው — በቤተሰቡ ውስጥ ዜና የሚያልፍበት መተላለፊያ
* የልጁ ቃል ኪዳን — ተለውጫለሁ፤ ያለፈውን ተወው፤ መምህሬ Cratippus እንደ አባት ሆኖ ነው የያዘኝ፤ ብዙ ጊዜ ከእሱ ጋር እራት እበላለሁ። ከዚያም፦ አባቴ እንዳዘዘኝ Gorgias የተባለውን መምህሬን ተውኩት
* Gorgias ለምን ተባረረ — የንግግር ጥበብ አስተማሪ ነበር፤ Cicero ልጁን ወደ መጠጥ ቤት እየመራው ነው ብሎ ጠረጠረው። ደብዳቤ ልኮ አቋርጠው አለው። ልጁ አቋረጠ — ቢያንስ በደብዳቤው ላይ
* ለምን አቴንስ? — በዚያ ዘመን ፍልስፍና የትምህርት መጨረሻ ነበር። አቅም ያለው ሮማዊ ወጣት ሰዋስው ተምሮ፣ የንግግር ጥበብ ተምሮ፣ ከሁሉ በኋላ ወደ ግሪክ ይላካል። ግሪክ በጦር ሜዳ ላይ ተሸንፋ ነበር፤ በአእምሮ ግን አልተሸነፈችም — የተሸነፈችው አገር ድል አድራጊዋን አገር ልጆች ታስተምር ነበር
* መራመድ የትምህርቱ አካል ነበር — Cratippus፣ Peripatetics ከሚባሉት ፈላስፎች በዘመኑ ግንባር ቀደሙ ነበር፤ Cicero ራሱ ከዚያ ትምህርት ቤት ካወቃቸው ሁሉ እሱን ያስበልጠዋል። የትምህርት ቤቱ ስም ከመራመድ የመጣ ነው፦ በተመሠረተበት ግቢ ውስጥ ጣሪያ ያላቸው የእግር መንገዶች ነበሩ፤ ትውፊቱ ደግሞ መምህራኑ ተቀምጠው ሳይሆን እየተመላለሱ ያስተምሩ ነበር ይላል
* ወጣት ሰው፣ ገንዘብ በእጁ — Marcus ወደ አቴንስ ብቻውን አልተላከም። ገንዘቡን የሚያስተላልፍ ሰው ነበር፤ ትምህርቱን የሚከታተል ሰው ነበር። አባቱ ከባሕር ማዶ ሆኖ ሪፖርት ይጠባበቅ ነበር
* አባት በሮም — በዚያው ዓመት ጸደይ ላይ Julius Caesar በምክር ቤቱ አባላት ተገደለ፤ ሥልጣኑ ወደ Mark Antony ገባ፤ እሱም የ Caesar ጄኔራልና የቅርብ ሰው ነበር
* ተነሣ — Cicero ስድሳ ሁለት ዓመቱ ነው። ከፖለቲካ ወጥቶ ነበር። ሊቀመጥ ይችል ነበር፤ ንብረት ነበረው፤ ዕድሜም ነበረው። ማንም አይጠብቅበትም። ተነሣና በምክር ቤቱ ፊት ቆሞ Antonyን በተከታታይ ንግግሮች ማጥቃት ጀመረ
* “Philippics” የሚለው ስም ራሱ ትንቢት ነው — ከዚያ ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት Demosthenes የተባለ ግሪካዊ ተናጋሪ ወደ ግሪክ እየተስፋፋ የነበረውን የመቄዶንያ ንጉሥ Philipን በተከታታይ ንግግሮች ተቃወመ፤ ንግግሮቹ “Philippics” ተባሉ። Demosthenes ተሸነፈ፤ ግሪክ ወደቀች፤ እሱም በመጨረሻ ራሱን አጠፋ። Cicero ይህን ሁሉ ያውቅ ነበር — የራሱን ንግግሮች በዚያ ስም የጠራቸው ራሱ ነው
* በአራት ሳምንት ውስጥ ሦስት መጻሕፍት — ኦክቶበርና ኖቬምበር ገደማ፣ በንግግሮቹ መካከል፣ ተቀምጦ ጻፈው። ሦስቱ አንድ ላይ ሆነው “De Officiis” ይባላሉ
* ስሙ ራሱ ችግር ነው — “Officium” በአንድ የአማርኛ ቃል አይያዝም። ግዴታ፣ ኃላፊነት፣ ተግባር፣ አንድ ሰው በሚይዘው ቦታ ምክንያት ከእሱ የሚጠበቅበት ነገር። ግሪኮች ለዚህ ሐሳብ የራሳቸው ቃል ነበራቸው፤ Cicero ደግሞ በላቲን መጻፍ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ቃል መርጦ በሮማውያን አንደበት ውስጥ ተከለው
* «ካልሆነ የተሻለ ቃል ስጠኝ።» — ምርጫውን ወዳጁ Atticus ተጠራጠረው። በኖቬምበር አጋማሽ የተጻፈው የ Cicero መልስ እስከ ዛሬ አለ፦ ግሪኮች “kathekon” የሚሉትን እኛ “officium” እንላለን፤ የቆንሲሎቹ officium፣ የምክር ቤቱ officium፣ የጦር አዛዡ officium አንልም ወይ?
* አንድ ሰው ሁለት ነገር ሲጽፍ — መጽሐፉ በደብዳቤ መልክ ተጽፎ ከመጀመሪያው መስመር ጀምሮ “አንተ” ይላል፤ ያ “አንተ” አቴንስ ውስጥ ያለው ወጣት ነው። ግን ጸሐፊው ስድሳ ሁለት ዓመቱ ነው፤ ሙያውን መርጦ ጨርሷል፣ ውሳኔዎቹን ወስኖ ጨርሷል፣ ውጤቱንም እያየው ነው፤ Antonyን መቃወሙ ሕይወቱን ሊያስከፍለው እንደሚችል ያውቃል። ስለዚህ መጽሐፉ ለወጣት የተጻፈ የሕይወት መመሪያና አንድ ሰው ሕይወቱን ሲያጠቃልል የጻፈው ሰነድ በአንድ ጊዜ ነው
ክፍል 2 — በግድግዳ ላይ የተጻፉ ስሞች (ኢብሳ)
* ሮም ንጉሥ አልነበራትም — የመጨረሻውን ንጉሥ ካባረረች ከአራት መቶ ዓመታት በላይ ተቆጥሮ ነበር። ሥልጣኑ በየዓመቱ ይለዋወጥ ነበር፤ ሁለት ሰዎች ተመርጠው ለአንድ ዓመት ይመሩና ይለቃሉ። “ንጉሥ” የሚለው ቃል በሮም ውስጥ ስድብ ነበር
* “የዘላለም አምባገነን” — Caesar ጦርነት አሸነፈ፤ ጦሩ ለምክር ቤቱ ሳይሆን ለእሱ ታማኝ ነበር። በሮም ልማድ አምባገነን የሚሾመው ለችግር ጊዜ ብቻ፣ ለስድስት ወር ነበር። “የዘላለም” የሚለው ቃል ሲጨመርበት ትርጉሙ ተቀየረ
* ማርች አጋማሽ — Caesar ወደ ስብሰባ ሲገባ በምክር ቤት አባላት ተከቦ በጩቤ ተወግቶ ወደቀ። ገዳዮቹ ራሳቸውን ነጻ አውጪ ብለው ጠሩ፤ ሁለቱ መሪዎቻቸው Brutus እና Cassius ይባላሉ
* ሴራው ተሳካ፤ የቀጣዩ ቀን ዕቅድ ግን አልነበረም — Caesar ሲሞት ተከታዮቹ አልሞቱም፤ ጦሩም አልፈረሰም። ገዳዮቹ ከከተማዋ ወጥተው ሸሹ፤ ከተማዋን ለአንድ ሰው ተዉለት
* አቅልለው ያዩት ሰው — Mark Antony ሰካራም ነው፣ ቁማርተኛ ነው፣ ትልቅ ሰው አይደለም ተባለ። ተሳስተው ነበር። የ Caesarን ወረቀቶች ያዘ፤ ገንዘቡን ያዘ፤ ወታደሮቹን ያዘ፤ ከዚያም ከተማዋን ያዘ። ምክር ቤቱ ዝም አለ
* የ Cicero እቅድ — Antonyን በቃላት ማግለል፣ ምክር ቤቱን ማንቃት፣ ጥንታዊውን ሥርዓት መልሶ ማቆም። ለዚያ ግን ሌላ ኃይል ያስፈልገው ነበር
* ዕድሜው ገና ያልደረሰ ወራሽ — Caesar ሕጋዊ ወንድ ልጅ አልነበረውም፤ በኑዛዜው የእህቱን የልጅ ልጅ Octavianን ልጁ አድርጎ ሰይሞ ነበር። Caesar ሲገደል ዐሥራ ስምንት ዓመቱ ነበር። ማዕረግ አልነበረውም፤ ስም ግን ነበረው — በዚያ ስም ወታደር መለመለ
* ሕይወቱን ያስከፈለው ዓረፍተ ነገር — Cicero ወጣቱን ደገፈው፤ ምክንያቱ ስሌት ነበር። ስለ እሱ ሲናገር “ወጣቱ መወደስ አለበት፣ ማዕረግ ሊሰጠው ይገባል፣ ከዚያም ወደ ጎን ሊደረግ ይችላል” የሚል ሐሳብ አቀረበ። ወጣቱ ይህን ሰማ
* ሦስት ሰዎች በአንድ ደሴት ላይ — በሚቀጥለው ዓመት መገባደጃ፣ በዛሬዋ ሰሜናዊ ጣሊያን ውስጥ Bononia አጠገብ፣ በወንዝ መካከል ባለች ትንሽ ደሴት ላይ Antony፣ Octavian እና Lepidus ተገናኙ። እርስ በርስ ስለማይተማመኑ ጦራቸውን በሁለቱም ወንዝ ዳርቻ አቁመው ራሳቸው ብቻ ተሻገሩ። ለቀናት ተነጋገሩ፤ ወጡና ሮምን ተከፋፈሉ
* “tresviri” — ሦስት ሰዎች — ራሳቸውን የሰየሙበት ስም ነው። ከዚያ የመጣው “triumvirate” የሚለው ቃል ዛሬም አለ፤ ትርጉሙ የሥልጣን ክብር ሳይሆን ቁጥር ነው። ምክር ቤቱ ተጠርቶ በሕግ አጸደቀው — ቃላት አሁንም ይነገሩ ነበር፤ ውሳኔው ግን ደሴቷ ላይ ተወስኖ ነበር
* “proscriptio” — በአደባባይ መጻፍ — “Scribere” መጻፍ፣ “Pro” በአደባባይ ማለት ነው። የተጻፈው ነገር የሰዎች ስም ነበር። ስምህ ከገባ፦ ሕጋዊ ጥበቃ የለህም፤ ንብረትህ ይወረሳል፤ የገደለህ ሰው ሽልማት ይከፈለዋል፤ ባሪያ ከገደለህ ነጻነት ይሰጠዋል
* አገሪቱ ዜጎቿን ለማደን ገበያ ከፈተች — ጎረቤትህ፣ ደንበኛህ፣ በቤትህ ውስጥ የሚሠራው ሰው ሁሉ በአንድ ጀንበር ሌላ ስሌት ያለው ሰው ሆነ
* ቁጥሩ ስንት ነበር? — ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በኋላ የጻፈው ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ Appian፦ ከምክር ቤቱ አባላት ሦስት መቶ ገደማ፣ ከሀብታሙ መደብ ሁለት ሺህ ገደማ። የሮሙ ታሪክ ጸሐፊ Livy ግን ከምክር ቤቱ አባላት መቶ ሠላሳ ብቻ ይቆጥራል — ምናልባት አንዱ የሸሹትንም ጭምር፣ ሌላው የተገደሉትን ብቻ ቆጥሮ ይሆናል። ዝርዝሩ የረዘመበት ምክንያት ሁለት ነው — ፖለቲካና ገንዘብ፤ ጦር ደመወዝ ይፈልጋል፣ የተወረሰ ንብረት ደግሞ ይሸጣል
* ሦስቱ ተለዋወጡ — Antony የራሱን አጎት አሳልፎ ሰጠ። Lepidus የገዛ ወንድሙን አሳልፎ ሰጠ። Octavian ደግሞ Ciceroን አሳልፎ ሰጠ — ማዕረግ ተሰጥቶት ወደ ጎን ሊደረግ የሚችል ልጅ ነው የተባለው ወጣት
* ሁለት ቀን — ከመቶ ሃምሳ ዓመት ገደማ በኋላ የታዋቂ ሰዎችን ሕይወት የጻፈው ግሪካዊው Plutarch እንደሚለው ስብሰባው ሦስት ቀን ቆየ፤ Octavian ለሁለት ቀን ስለ Cicero ተከራከረ፤ በሦስተኛው ቀን ተወው ይባላል
* ከሦስቱ ስሞች የሞተው አንዱ ብቻ ነው — የ Antony አጎት ወደ እኅቱ ቤት ሸሸ፤ እሷ የ Antony እናት ናት፤ ከልጇ ምሕረት አስገኘችለት። የ Lepidus ወንድም ወታደሮቹ ሳያስቆሙት አመለጠ። ሦስተኛው ስም የ Cicero ነበር
* “fides” የተባለው ቃል — ትርጉሙ ቃል መጠበቅ፣ እምነት የሚጣልበት መሆን ማለት ነው። ሮማውያን ግዛታቸው የተገነባው በሰይፍ ብቻ ሳይሆን በዚህ ላይ ነው ብለው ያምኑ ነበር። እናም ያንን ቃል በሚናገሩ ሰዎች ከተማ ውስጥ ሦስት ሰዎች ተቀምጠው ዘመዶቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ይለዋወጡ ነበር። Cicero ስለ ግዴታ የጻፈው በዚህ ልዩነት መካከል ነው
* ውጤቱ ሳይታወቅ የተጻፈ — መጽሐፉ ሲጻፍ ገና ዝርዝሩ አልወጣም ነበር። የተጻፈው ውጤቱ ከታወቀ በኋላ አይደለም
* ያ ዓመት እንዴት አለቀ — የዚያ ዓመት ዲሴምበር ላይ ወታደሮች Ciceroን ከገጠር መኖሪያው አጠገብ ደረሱበት፤ ወደ ባሕሩ ሊያመልጥ ሲሞክር ነበር። ባሪያዎቹ በአልጋ ተሸክመው ይወስዱት ነበር፤ ሊከላከሉለትም ፈልገው ነበር። እሱ ግን ከለከላቸው — አልጋውን መሬት ላይ አስቀምጡ አላቸው፤ ጭንቅላቱን አውጥቶ አንገቱን ዘረጋ። ስድሳ ሦስት ዓመቱ ነበር
* ትእዛዙ በዚያ አላበቃም — ጭንቅላቱንና ንግግሮቹን የጻፈችውን እጁን ቆርጠው ወደ ሮም ወሰዱ። በሮም አደባባይ መካከል ሮማውያን ወደ ሕዝብ ሲናገሩ የሚቆሙበት መድረክ ነበር፤ ያ ሰው ዕድሜውን ሙሉ ከዚያ ላይ ተናግሯል። Antony ጭንቅላቱንና እጁን በዚያ መድረክ ላይ እንዲሰቀሉ አዘዘ
* ቤተሰቡም አልተረፈም — ወንድሙ Quintus እና የወንድሙ ልጅ በዚያው ሰሞን በዚያው ዝርዝር ምክንያት ታደኑ። የ Quintus ልጅ አባቱ የተደበቀበትን ቦታ በስቃይ ውስጥም አልተናገረም። Quintus ይህን ሲሰማ ልጁን ለማዳን ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ሁለቱም ተገደሉ
* ልጁ አቴንስ አልነበረም — Caesarን ከገደሉት መሪዎች አንዱ Brutus ወደ አቴንስ መጥቶ እዚያ የሚማሩትን ወጣት ሮማውያን ሲሰበስብ የ Cicero ልጅ አብሮት ተሰልፎ ነበር። የልጁም ስም በዚያው ዝርዝር ውስጥ ገብቶ ነበር። መጽሐፉ ግን ቀድሞ ተጽፎ አልቆ ነበር፤ ልጁ መቼ እንደደረሰውና መቼ እንዳነበበው የሚነግረን ሰነድ የለም
ክፍል 3 — መዝገቡ፦ አራት ምሰሶና ሦስት ጉዳይ (አበባ)
መጽሐፉ ከየት መጣ
* Panaetius — ከ Cicero ከመቶ ዓመታት ገደማ በፊት የነበረ፣ ከሮዶስ ደሴት የመጣ ግሪካዊ ፈላስፋ፤ ሮም ውስጥ ኖሮ ነበር። Stoic ከሚባለው ወገን ነው — ዓለም ሥርዓት አላት፣ ሰውም ቦታው የሚጠይቀውን ሊወጣ ይገባል የሚሉ
* ያልተጻፈው ሦስተኛ ክፍል — ስለ ግዴታ የጻፈውን ሥራ በሦስት ክፍል እከፍለዋለሁ ብሎ አስቀድሞ አስታወቀ። የመጀመሪያውን ጻፈ። ሁለተኛውንም ጻፈ። ሦስተኛውን አልጻፈም። ከዚያ በኋላ ሠላሳ ዓመት በሕይወት ኖረ — ይህን የመዘገበው የራሱ ተማሪ Posidonius ነው — ሦስተኛውን ግን አልጻፈውም
* ያልተጻፈው ክፍል ርዕስ — ትክክለኛው ነገርና አዋጭ የሆነው ነገር በተጋጩ ጊዜ ምን ይደረግ የሚለው
* Cicero ራሱ ይነግረናል — ለመጀመሪያዎቹ ሁለት መጻሕፍቴ Panaetiusን ተከትያለሁ ይላል፤ ሦስተኛውን ግን ማንም አልጻፈውም፣ ስለዚህ ያለ ምንም ድጋፍ በራሴ ጉልበት እጽፈዋለሁ ይላል።
ሦስቱ መጻሕፍት፣ ሦስቱ ጥያቄዎች
* መጽሐፍ አንድ፦ “ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው?” — በላቲን “honestum”፤ የተከበረ፣ የሚያምር፣ ማፈሪያ የሌለበት ማለት ነው
* መጽሐፍ ሁለት፦ “የሚጠቅመው ነገር ምንድን ነው?” — አንድ ሰው ድጋፍ እንዴት ያገኛል? ሰዎች እንዴት ይተማመኑበታል? ስም እንዴት ይገነባል? መልሱ አጭር ነው፦ ለአንድ ሰው ከሁሉ የሚበልጠው ሀብት ሌሎች ሰዎች ናቸው። መሬትም አይደለም፣ ገንዘብም አይደለም፣ ጦርም አይደለም
* መወደድና መፈራት — ሥልጣንን የሚያስጠብቁ ሁለት መንገዶች ናቸው። መወደድ ይበልጣል፤ መፈራት ከሁሉ የራቀ ነው። ምክንያቱን ሲያስረዳ ከአንድ የቀድሞ ሮማዊ ገጣሚ ሁለት መስመር ይጠቅሳል፦ “የሚፈሩትን ይጠሉታል። የሚጠሉት ሰው ደግሞ እንዲሞት ይመኙታል”። ከዚያም ይጨምራል — የብዙዎችን ጥላቻ ተሸክሞ ሊቆይ የሚችል ሥልጣን የለም፤ ይህ ቀድሞ ባይታወቅ እንኳ አሁን ታውቋል
* መጽሐፍ ሦስት፦ ሁለቱን ማጋጨት — ትክክለኛውና የሚጠቅመው ወደ ተለያየ አቅጣጫ በሚጐትቱበት ቀን ምን ይደረግ? መልሱ ከመጀመሪያው መስመር ግልጽ ነው፦ እንዲህ ያለ ቀን የለም። ግጭቱ ራሱ ማታለል ነው። ክፉ የሆነ ነገር ጠቃሚ ሆኖ አያውቅም። ቀሪው መጽሐፍ ያንን ዓረፍተ ነገር ማስረዳት ነው
አራቱ ምሰሶዎች
* ጥበብ — እ…